በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአንድ ጀንበር ከ10 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ይተከላሉ
የዘንድሮው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል ሐምሌ 27/2018 ዓመተ ምህረት የሚካሄድ ሲሆን፣ በእለቱ ከ10 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉም ተገልጿል።
የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አስመልክቶ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ እና የደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በመግለጫው፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ባለፉት ሰባት አመታት ሲተገበር መቆየቱን ጠቅሰው፣ መርሃ ግብሩ ትልቅ ሀገራዊ ተልኮ ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመርሃ ግብሩ የህዝብ ተሳትፎና ባለቤትነት የተረጋገጠበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ስነ ምህዳራዊ ጠቀሜታው ጉልህ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ጠቁመዋል።
ባለፉት አመታት እንደ ሀገር ከ48 ቢሊዮን በላይ እንደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መትከል መቻሉን አቶ ኡስማን ገልፀዋል።
በዘንድሮው የአንድ ዘንጀንበር አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንደ ሀገር ከ800 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደ ክልል ደግሞ ከ10 ሚሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉም አመላክተዋል።
በክልሉ በተዘጋጁ 247 ቦታዎች የተከላ መርሃ ግብሩ የሚከሄድ መሆኑን አቶ ኡስማን ጠቅሰው፣ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይሳተፍበታልም ብለዋል።
ለዚህም የጉድጓድ ቁፋሮና የችግኝ ዝግጅት ስለመጠናቀቁም አቶ ኡስማን ጠቁመው፣ በእለቱ ኑ ተስፋን እንትከል በማለትም ለመላው የክልሉ ህዝብ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም መጫ በበኩላቸው፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት ሂደት የአረንጓዴ አሻራ ድርሻ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።
የምግብ ዋስትናንና ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ፣ የአካባቢን ስነ ምህዳርን በማስጠበቅ ብልም ከአየር ንብረት ጋር ተያየዞ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ረገድ አረንጓዴ አራሻ የሚጫወተው ሚና በእጅጉን የጎላ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞች ለተኪ ምርም፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት፣ ለውጭ ገበያ እንዲሁም ለስራ እድል ፈጠራ ጠቀሜታቸው ላቅ ያለ መሆኑንም አቶ አብርሃም ጠቁመዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገር ዲፕሎማሲና ገፅታ ግንባታ ረገድ የሚኖረው ፋይዳ የላቀ መሆኑንም አብራርተዋል።
በመርሃ ግብሩ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን፣ አብሮነትና ወንድማማችነት የሚጠናከርበት ስለመሆኑም ተገልጿል።
Central Ethiopia Regional Government Communication Affairs bureau

